አልወድሽም እንጂ ባለፈው እንዳልኩሽ
አልወድሽም እንጂ እኔ ከወደድኩሽ
እኔ ያንቺ እያለሁ አንቺ የኔ እያለሽ
ሲኦል ነው መድረሻው አፈቀርኩሽ ያለሽ
እንኳንስ ሊነኩት ቢያዩት ያንቺን ገላ
አለቀለት በቃ ሃገሩ በሙላ::
አልወድሽም እንጂ
ምን ብየ ልንገርሽ በየትኛው ቋንቋ
የኛ መከፋት ነው የዚች አለም ጭንቋ
ደስታችን ክብሯ ነው ፍቅራችን መልህቋ::
ምዬ ተገዝቼ ነግሬሽም የለ
ላንቺ ያልኩት ፍቅር በልቤ ውስጥ ካለ
ደመና ላይ ሆነን ኮከብ እንቆጥራለን
ውቅያኖስ አንጥፈን ግብር እንጠራለን
ከፀሃይ የሚልቅ ብርሃን እንፈጥራለን
ሲያሻን ተረማምደን ሲያሻን እንበራለን::
አልወድሽም እንጂ እኔ ከወደድኩሽ
ያው እንደነገርኩሽ
ከቤታችን ጓዳ ሰላም የማይጠፋ
ክርና መርፌ ነን ፍቅርን የምንሰፋ
ኮከብና ሰማይ ቀለምና ሸራ
በቃል ተዋህደን ውበት የምንዘራ
ምን አባቴን ላርግሽ
እውነቱን ስነግርሽ
አልወድሽም እንጂ እኔ ከወደድኩሽ
አእዋፋት ከዱራቸው ዜማ ይደርሳሉ
ከዋክብት ከሰማይ ቁልቁል ይወርዳሉ
እንስሳቱ ሁሉ እኛን ይከባሉ
ሌሊት በጨለማ ይደምቃል ሰማዩ
እኛን ሲያይ ይውላል ሰው ያለጉዳዩ ::
አልወድሽም እንጂ ድንገት ከወደድኩሽ
ደጋግሜ እንዳልኩሽ
ሁሉን እንሆናለን የማንችለው የለም
እኔ ከወደድኩሽ ትሞላለች አለም::
Comments
Post a Comment