በተለምዶ ድብርት/ድባቴ በህክምናው አጠራር (Major depressive disorder) በመባል የሚታወቀው የጤና እክል የህመሙ ተጠቂ በሚያስበው ሀሳብ፣በሚከውነው ድርጊትና በሚሰማው ስሜት ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድር ከባድ እና አብዛኛው ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ህመም ነው። መልካሙ ዜና ደግሞ ህክምና ያለው ህመም መሆኑ ነው። ድባቴ ሁል ጊዜ የሀዘን ስሜት እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል ወይም ደግሞ በፊት ፍላጎት(Interest) የነበረን ነገሮች ላይ የነበረንን ፍላጎት እንድናጣ ሊያደርግ ይችላል።ወይም ፍላጎት ማጣቱንና የሀዘን ስሜትን አንድ ላይ አጣምሮ ሊይዝ ይችላል። ከዚህም የተነሳ በተጠቂው ግለሰብ የስራ ህይወቱ ላይም ሆነ የግል ህይወቱ ላይ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጫና በማሳደር ሰውዬው በትክክል እንዳይንቀሳቀስ ወይም እንዳይሰራ ብዙ ችግር ያስከትላል።
የድባቴ ምልክቶች ከቀላል እሰከ ከፍተኛ ሊደርሱ የሚችሉ ሲሆን እነዚህን ያካትታሉ።
- የሀዘን ወይም የድብርት ስሜት መሰማት
- በፊት ደስ ይሉን የነበሩ እና ፍላጎት የነበረን ነገሮች ላይ የነበረንን ስሜት ማጣት
- የአመጋገብ ስርዓት ለውጥ- ያልተፈለገ የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ
- የእንቅልፍ ማጣት ወይም ከመጠን በላይ መተኛት
- አቅም ማጣት እና ከፍተኛ የድካም ስሜት
- ያለ ምክንያት ሰውነትን ማንቀሳቀስ (ለምሳሌ እጅን ማወናጨፍ ) ወይም ዘገምተኛ የሆነ አነጋገር እና እንቅስቃሴ( ይህ የሚስተዋለው በሌሎች ግለሰቦች ነው።)
- የጥፋተኝነት ስሜት እና ራስን ዋጋ ቢስ አድርጎ ማሰብ
- ለማሰብ አትኩሮት ለመሰብሰብ እና ውሳኔዎችን ለማሳለፍ መቸገር
- ስለ ሞት እና ራስን ስለማጥፋት አብዝቶ ማሰብ
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት የሚቆዩ ከሆነ ድባቴ ነው ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በሌሎች ህመሞችም ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው። (የእንቅርት በሽታ፣የጭንቅላት እጢ፣የቫይታሚን እጥረት) ተመሳሳይ ምልክቶች የሚያሳዩ ስለሆነ በተለያዩ ምርመራዎች የእነርሱ አለመኖር መረጋገጥ አለበት።
በአመት ውስጥ ድባቴ ከአስራ አምስት ሰዎች አንዱን ያጠቃል።(6.5%) በህይወት ዘመን የሆነ ጊዜ ከስድስት ሰዎች አንዱ(16.6%) ይጠቃል። ድባቴ በየትኛውም የእድሜ ክልል ሊጀምር የሚችል ቢሆንም በብዛት የሚጀምረው 18 እስከ 25 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ነው። ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ድባቴ ከመርዶ የተለየ መሆኑ
የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን፣ስራችንን ስናጣ ወይም ከፍቅር አጋራችን ጋር ስንለያይ ለመቋቋም ከባድ የሆነ ሀዘን ሊሰማን ይችላል። በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች የሚኖር የሀዘን ስሜት ጤናማ እና የሚጠበቅ ነው። የሚወዱትን ያጡ ሰዎች ራሳቸውን ድባቴ ውስጥ እንዳሉ ሊገልፁ ይችላሉ።
ነገር ግን ሀዘንና ድባቴ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ሀዘን ተፈጥሮአዊ ሂደት ሲሆን ለእያንዳንዱ ግለሰብ ለየት ያለ ባህርይ ሊኖረው ይችላል። ከድባቴ ጋርም በአንዳንድ ነገሮች ተመሳሳይነት አለው። መርዶም ሆነ ድባቴ ከፍተኛ የሆነ የሀዘን ስሜት እና ለነገሮች የነበረንን ፍላጎት እንድናጣ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህ ቀጥሎ ልዩነታቸውን እናያለን።
- በመርዶ የሚያሰቃዩ ስሜቶች የሚመጡት እንደ ሞገድ ነው።(የሚሄድ እና የሚመጣ) ብዙ ጊዜ ከሟች ጋር ካሳለፍናቸው መልካም ትዝታዎች ጋር ይደባለቃሉ። በድባቴ ግን ለሁለት ሳምንት እና ከዚያ በላይ ያለማቋረጥ የሀዘን ስሜት እና ፍላጎት ማጣት ይከሰታል።
- በመርዶ ጊዜ ለራሳችን የምንሰጠው ክብር አይለወጥም። በድባቴ ግን ራሳችንን ዋጋ-ቢስ አድርገን እናስባለን።
- በአንዳንድ ሰዎች የሚወደውን በሞት መነጠቅ ድባቴ ሊያስከትል ይችላል። አንዳንዶች ስራ ማጣት እና የአካል ጥቃት የድባቴ ሰለባ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል።
አጋላጭ ሁኔታዎች(Risk factors)
ድባቴ ማንም ላይ ሊከሰት ይችላል። በጣም ጥሩ ህይወት በሚመሩ ሰዎች ላይ ጭምር
ብዙ ነገሮች በድባቴ ላይ አስተዋፅኦ አላቸው
- በአዕምሮአችን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቅመሞች መጠን መዛባት
- በዘር የመተላለፍ እድል አለው። ተመሳሳይ መንትዮች(Identical twins) አንደኛው ከተጠቃ ሌላኛው የመያዝ እድሉ 70% ነው።
- ለራሳቸው ዝቅተኛ አመለካከት ያላቸው፣በውጥረት ከልክ በላይ የሚረበሹ እና በአጠቃላይ ደግ ነገር ይገጥመኛል ብለው የማያስቡ ሰዎች ለድባቴ ተጋላጭ ናቸው።
- የጥቃት እና የአመፅ ሰለባ የሆኑ፣ ትኩረት የተነፈጋቸው ሰዎች ለድባቴ ተጋላጭ ናቸው።
ድባቴ እንዴት ይታከማል?
ድባቴ ከአብዛኞቹ የአዕምሮ ህመሞች የተሻለ ሊታከም የሚችል ህመም ነው። ከ 80%-90% የሚሆኑ የድባቴ ተጠቂዎች ከታከሙ ጥሩ መሻሻል ያሳያሉ።ከታከሙ ከሞላ ጎደል ሁሉም ህመምተኞች በምልክቶቹ ላይ ለውጥ ይኖራቸዋል።
መድሃኒቶች
የአዕምሮ ኬምስትሪ በህመሙ ላይ የራሱ ተፅእኖ ስለሚኖረው ያንን ለማስተካከል ፀረ-ድባቴ(antidepressant) መድሃኒቶች እንጠቀማለን። ፀረ-ድባቴ መድሃኒቶች መድሃኒቱን መጠቀም በተጀመረ በመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ሳምንት የተወሰነ መሻሻል እንዲኖር ያደርጋሉ። ነገር ግን ሙሉ ጥቅማቸው እስከ ሁለት ወር ድረስ ላይታይ ይችላል። ነገር ግን ለበርካታ ሳምንታት መድሃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ለውጥ የማይኖር ከሆነ ወይም የጎንዮሽ ጉዳት ካለው መድሃኒቱ በሌላ እንዲተካ ወይም መጠኑ(dose) እንዲስተካከል ሳይካትሪስቱን ማማከር
ተገቢ ነው።
ፀረ-ድባቴ መድሃኒቶችን ምልክቶች ከጠፉ በኋላ ለስድስት ወር እና ከዚያ በላይ እንዲወሰድ ሳይካትሪስቶች ይመክራሉ። ይህ ህመሙ ዳግም እንዳያገረሽ ይጠቅማል።
ሳይኮቴራፒ
ለቀላል ድባቴ ብቻውን ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ለሆነ ድባቴ ደግሞ ከፀረ-ድባቴ መድሃኒት ጋር አንድ ላይ ይሰጣል። ህክምናው ትኩረቱን የሚያደርገው ህመምተኛው የተዛቡ ሀሳቦቹን እንዲገነዘብ በማድረግ እና ሀሳቡን አና ድርጊቱን እንዲያስተካክል በመርዳት ነው።
ኤሌክትሮ ኮንቨልሲቭ ቴራፒ
ይህ ለህመምተኛው ማደንዘዣ በመስጠት አዕምሮን በኤክትሪክ በማነቃቃት ሲሆን በሳምንት ሶስት ጊዜ በአጠቃላይ ከ 6-12 ጊዜ የሚደረግ ነው።
በድባቴ የተጠቃ ሰው ምን ማድረግ አለበት?
በድባቴ የተጠቃ ሰው ምልክቶቹን ለመቀነስ ማድረግ ያለበት በርካታ ነገሮች አሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት እና አልኮል አለመጠጣት።
ድባቴ እንደየትኛውም ህመም በሽታ ነው። ህክምናም አለው። ምልክቶቹን ካስተዋሉ ሀኪም ያማክሩ።
Comments
Post a Comment